ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት/ንጉሰ ጎጃም ወከፋ/
ንጉስ ተክለሃይማኖት እና አደዋ ትልቅ ቁርኝት አላቸዉ---------------------------------------------------------------------------------------ንጉስ ተክለሃይማኖት የጎጃም ጦር ይዘዉ ወደ አደዋ በመዝመት የድሉ አንድ አካል ናቸዉ፡፡-------------------------------------
የንጉሥ ተክለ ሀይማኖትን ታሪክ ለማወቅ የጎጃም ገዥዎችን ታሪክ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የጎጃም አገረ ገዥዎች ታሪክ የሚጀምረው ከደጃዝማች ዮሴዴቅ (1744 - 1749) እንደሆነ በርካታ ታሪክ ፀሐፊዎች ዘግበውታል፡፡ ዮሴዴቅ በዳግማዊ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ (1664-1699) ዘመን ለማዕከላዊ መንግስት አልገብርም ብሎ ከማስቸገር አልፎ እስከ ጨጨሆ በር ድረስ እየጋለበ ለጎንደር ቤተ መንግስት ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራን በመጥቀስ ዶ/ር ሥርግው ገላው ጽፈዋል፡፡ ኢያሱም የዮሴዴቅን ኃያልነት ካየ በኋላ ልብ ሊይዝ የእናቱን ልጅ ዳግማዊት ወለተ እስራኤልን ዳረለት፡፡ (አለቃ ተክለ ኢየሱስ፣2008፡20)
ወለተ እስራኤል የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ ናቸው፡፡ “ቋረኛዋና ጥሩይቱ እቴጌ ምንትዋብ የአፄ ባካፋ ባለቤት በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ለሰላሳ ዓመት አስተዳድረዋል፡፡ አፄ ባካፋ በወጣትነታቸው ሰለሞቱ ከሁለቱ የተወለደው ቀጣዩ ንጉሥ ኢያሱ ዓለም ሰገድ ነግሦ እቴጌ ምንትዋብ በሞግዚትነት መንግስቱን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ እቴጌ ምንትዋብ ወጣት ሰለነበሩ ከምልምል ኢያሱ ሦስት የሚያማምሩ ልጆችን ወለዱ፡፡”(ጥላሁን ብርሃን፣2008፡33)
እነሱም ወለተ እስራኤል፣ አስቴርና አልጣሽ ናቸው፡፡ ምንትዋብ የተጠቀሱትን ሴት ልጆቿን ለታዋቂ ኢትዮጵያውያን መሳፍንት በመዳር ግዛቷንና የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ተጠቅማባቸዋለች፡፡ ከተጠቀሱት ውስጥም ወለተ እስራኤልን ለጎጃሙ ገዥ ደጃዝማች ዮሴዴቅ ተድራ ኃይሉን ወልዳለች፡፡ (አለቃ ተክለ ኢየሱስ፣2008፡22)
የንጉሥ ተክለ ሀይማኖት የዘር ሀረግም የሚመዘዘው ከዚህ ትውልድ ነው፡፡ ዮሴዴቅ ታላቅ ኃይሉን ይወልዳል፣ ታላቅ ኃይሉ መርድን እና ድንቅነሽን ይወልዳሉ፣ ድንቅነሽ የዳሞቱን ባላባት ደጃዝማች ዘውዴ ስልን አግብተው ደጃዝማች ጎሹን ወለዱ፣ ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ደግሞ ደጃዝማች ተሰማን፣ ደጃዝማች ብሩን፣ ደጃዝማች ንጉሴን፣ ልጅ ይማምን ይወልዳሉ፡፡ ደጃዝማች ተሰማ ጎሹ ራስ አዳልን (ንጉሥ ተክለ ሀይማኖትን) ወለዱ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው አዳል (ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት) የተሰማ ጎሹ ልጅ ነው፡፡ ልጅ አዳል የእናቱ አገር በደብረ ኤልያስ ወረዳ ገነት አቦ ይባላል፡፡ ፊት ትቤ አቦ ይባል ነበር፡፡ ይህችም የልጅ አዳል እናት ወይዘሮ ምዕላድ ነገዷ ከአፄ እስክንድር የማርታ፣ የቴዎድሮስ፣ የዓመተ ክርስቶስ፣ የዕርቄ፣ የኢዮልያ፣ የቱፋ፣ በቋ ልጅ ናት፡፡ (አለቃ ተክለኢየሱስ፣2008፡219). ልጅ አዳል በሕፃንነቱ አያቱ ጎሹ በካሳ ኃይሉ (አፄ ቴዎድሮስ) ከተገደሉበትና አባቱ ተሰማ ጎሹ ከተጋዘ በኋላ ዘመድ የጭንቅ ዕለት ነውና በአባቱ አደራ ባይነት ወደ አጎቱ ተድላ ጓሉ የቀድሞዋ መንቆረር ያሁኗ ደብረ ማርቆስ ተልኮ ከልጆቹ ከንጉሴና ከደስታ ጋር እየተማሩ አደጉ፡፡
ከዚያ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት የጎጃም ገዥ ለመሆን ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡
በቀድሞዋ መንቆረር በአሁኗ ደ/ማርቆስ የሚገኘዉ የጎጃም ገዥዎች ቤተመንግስት በ1845 ዓ/ም ደጃዝማች ካሳ(ኋላ ዳግማዊ ቴዎድሮስ) የጎጃምን ግዛት ለማደላደል ዘመቻ አድርገው ክረምት በ1845 መንቆረር(አሁን ደብረ ማርቆስ) ውስጥ ቤተ መንግስቱ በሚገኝበት ቦታ የሳር ሰቀላ ቤቶችን አሰርተው መክረማቸውና በቦታውም ከተማ እንዲቆረቆር ትዕዛዝ ሰለማስተላለፋቸው የቤተመንግስቱ ጅማሬም ለደጃዝማች ካሳ እና ለደጃዝማች ተሰማ ጎሹ/የንጉስ ተክለሃይማኖት አባት/ መካረሚያ ከተሰሩ ጎጆች እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሰቀላ ጎጆዎች የተመሰረተ ሲሆን በእነዚህ ሰቀላ የሳሪ ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን እድሳት በማከናወን ደጃች ተድላ ጓሉ(1847-1860)፣ ደጃች ንጉሴ ተድላ(1860)፣ ደጃዝማች ደስታ ተድላ(1860-1861) እንደ ሁኔታው ጎጃምን ሲገዙ ቆይተውበታል፡፡ ከደጃዝማች ደስታ ተድላ በኋላ ጎጃምን የገዙት ራስ አዳል ተሰማ(ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት) በዘመናቸው የቤተ-መንግስቱን የውስጥ አደረጃጀት በማስፋፋት የአስተዳደር ስራ በተደራጀ መንገድ እንዲከናወን በመደረጉና በሳር ክዳን ሰፊና ትልቅ አዳራሽ አሰርተው ሰለነበር በአካባቢው ማህበረሰብ የንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ቤተ መንግ
ስት በሚል ስያሜ መጠራት እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ሥያሜው ከንጉሥ ተክለ ሀይማኖት በኋላም ሳይለወጥ የአሁኑን ዘመን ደርሷል፡፡
ራስ አዳል ተሰማ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ጥር 13 ቀን 1873 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ‹‹ንጉሠ ከፋ ወጎጃም›› ተብለዉ የሸዋው ንጉስ ምኒሊክ በተገኘበት ነገሡ (ተክለጻድቅ፣200፡59)፡፡ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ራስ አዳል ተሰማ ከንግሥና በኋላ ያከናወኗቸውን ተግባራት እንዲህ ዘግበውታል፡፡“ንጉሥ ተክለ ሀይማት በጎጃምና በከፋ ነግሦ ከመጣ በኋላ በጎጃምና በዳሞት ሹም ሽር አደረገ፡፡ የበኩር ልጁን በዳሞት ራስ በዛብህ አሰኘ፤ ቀጥሎ ደግሞ በአፄ ዩሐንስ ፈቃድ ጎጃምን ወረዳ በመንቆረር በዘና ታቦተ ማርቆስን ተክሎ ደበረ፡፡ ብዙ ቅፈፍ አግብቶ 318 ደብተራ ሰራለት፡፡ መልዕልተ አድባር (ከአድባራት በላይ) ይሁን አለ፡፡ ደብረ ማርቆስ ይባል እንጅ መንቆረር አይባል ብሎ አዋጅ ነገረ፡፡ አለቃ መልአከ ፀሐይ መሸሻን፣ ሊቀ ጠበብት ጽሐፌ ትዕዛዝ እሸቴን ሾመ፡፡ ለጥንት ባላአፈሮችም ለመንቆረርና ለዝና ልጆች የዣባጢን የጮቢ የሚባል ሀገር ምንጣፍ ተክቶ ሲሶ ግብዝና ለርሱ፣ ሁለት እጅ ለጥንት ባላአፈሮች ሰጠ፡፡” (የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 263)
ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ ከጎጃም የስልጣን ተቀናቃኞቻቸው ጋር እና ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር በርካታ ጦርነቶችን አካሂደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሱዳን ደርቡሾች ድንበር ተሻግረው ጎንደር ድረስ በመግባት ጥር 10 ቀን 1880 ዓ/ም ቤተክርስቲያን አቃጥለው ቀሳውስቱንና ሲያርዷቸውና እንዲህ ተብሎ ሲገጠም፡-
ተከተልኸኝ ብየ ዞሬ ዞሬ ሳይ፣
ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጎንደር ቀረህ ወይ?
ወገራ አሳላፊ ደንቢያ እንጀራ ጣይ፣
ተበላህ ጎንደሬ አተትነሳም ወይ?
በወቅቱ አጼ ዮሐንስ አስመራ ስለነበሩ ይህንን በቀል ንጉስ ተክለ ሀይማኖት እንዲበቀል መልክት በመላካቸው ንጉስ ተክለ ሀይማኖት 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) የሚሆን ሰራዊታቸውን ይዘው በመሄድ ድል አድርገዋል ምንም እንኳን በሁለተኛው ዘመቻ ወቅት ቢሸነፉም (ተክለጻድቅ፣2000፡6)፡፡ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት በር በከፈተው ታላቁ የአድዋ ጦርነት ወቅትም የጎጃምን ጦር በመምራት 3000 (ሦስት ሺህ) ሰራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል (ተክለጻድቅ፣2000፡109፤ መሪራስ አማን፡2009፡355)፡፡ የግዛት ዘመናቸውም ራስ አዳል ተሰማ ተብለው ከ1861-1872 ዓ/ም ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ተብለው ከ1873-1893 ዓ/ም በድምሩ ለ32 ዓመት ጎጃምን ገዝተዋል፡፡ በአጠቃላይ በዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ለራሳቸውና ለሀገራቸው ጎጃም ሲፈፅሙ ኑረው ጥር 3 ቀን 1893 ዓ/ም በእለተ አርብ ደብረ ወርቅ ላይ አረፉ፡፡እነሆ የጎጃም መገለጫ የሆኑት ሀገር ወዳዱ እኒህ ታላቅ ንጉስ ካረፉ ዛሬ 118 ዓመታቸዉ ነዉ፡፡ሁሌም በየዓመቱ ጥር 3 ቀን እሳቸዉ በመሰረቱትና አጽማቸዉ በሚገኝበት መልዕልተ አድባር ደብረ ጸሃይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን መታሰቢያ ይደረግላቸዋል፡፡የአባቶቻቸን ልጆች እንሁን መልዕክታችን ነዉ!