• 07 Nov, 2024

በላይ ዘለቀ ማናቸው ? ትውልዳቸውስ

በላይ ዘለቀ ማናቸው ? ትውልዳቸውስ

በላይ ዘለቀ ማንነት እና ታሪክ

inbound1757084201452990506
የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ማንነት

ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በፋሽስት ዘመን ጎጃም ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አራት የአርበኛ መሪዎች መካከል አንዱ ነበር። በጎጃም ውስጥ ሲካሄድ ስለነበረው ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ ስሙ እየተደጋገመ የሚወሳው የበላይ ዘለቀ ስም ብቻ ስለሆነ የሌሎቹ የጎጃም አርበኛ መሪዎች ስምና ስራ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ዘንድ አይታወቅም። ሶስቱ የጎጃም ታላላቅ አርበኛ መሪዎች ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህና ራስ ኃይሉ በለው ናቸው። በነዚህ አርበኞች ስር እልቆ ቢስ ስመጥር አርበኞች ነበሩ።

የዛሬው ቀን በላይ ዘለቀ የተሰጠውን ምህረት ባለመጠቀሙና የወቅቱ አቃቢ ሕግ የነበሩት አርበኛው ደጃዝማች ታከለ ወለደ ሐዋርያት ያቀረቡበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤት በስቅላት እንዲቀጣ የወሰነበትና የተሰቀለበት እለት በመሆኑ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በትውልድ ሐረጉ ዙሪያ የሚስተጋባውን ውዥንብር እናጠራለን።    

ባለፈው ሰሞን «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ግጥም ያለው እነ ጃዋር መሐመድ ስፖንሰር ያደረጉት ዘፈን ተለቅቆ ነበር። የግጥሙ «ሀሳብ» ባለቤት የዕውቀት ጾመኛው የወያኔው ሹም ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ተስፋዬ ገብረአብን በቡርቃ ዝምታ ድርሰቱ የሚተቹት «ኢትዮጵያዊ ነን» የሚሉ አንዳድን ፕሮፌሰሮችም ባለፈው ሰሞን ሲያትል ላይ በተካሄደ አንድ ጉባኤ ላይ ተስፋዬ ገብረአብ ስለበላይ ዘለቀ ኦሮሞነት የተናገረውን በማስተጋባት ተስፋዬን ለምስርክነት አብቅተውታል። ለወትሮው ምሑርነት ማለት አቀራረቡ በማስረጃ የዋጀና ጭብጡ በዶሴ የተፈተገ ዕውነት ነጋሪ ነበር። ዘንድሮ ግን ምሑርነት ማለት ለሰይጣናዊ ዓላማው አገር ለማፍረስ በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ሐውልት የቆመለት ልብ ወለድ የደረሰው ተስፋዬ ገብረአብ የፈጠረውን ታሪክ አገር ለማዳን ተሰበሰብን ብለው የአገር አፍራሹን ሤራ ለምስክርነት የሚያስቆጥር የዓይነ ኅሊና እና የእዝለ ልቦና ወታወር ሆኗል።

ተስፋዬ ገብረአብ የሚባለው የወያኔው ሹም ከሁለት ዓመታት በፊት በተካነበት የእባብ ልቡ እየተሳበ «በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው፤ ሙሉ ስሙም በላይ ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ ይባላል» ሲል በሬ ወለደ ፈጠራ ጽፎ ነበር። ተስፋዬን ተቀብለው የኦነግ «ዶክተሮች» የወዲ ገብረ አብን ፈጠራ በስፋት አስተጋቡ። ለሚታዘብ ሁልጌዜ የሚገርመው የኦነግ «ዶክተሮች» ተስፋዬ ፈልስሞ እንካችሁ የሚላቸውን ሸቀጥ «ምንጭህ ከምን?» ብለው ሳይጠይቁ እንደወረደ ሀቅ አድርገው መቀበላቸው ነው። ተስፋዬ የወያኔ ፕሮጀክቶች የሆኑትን «የቡርቃ ዝምታን» እና «ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድን» የጻፈው በዚህ መልክ በበሬ ወለደ ነበር። ለነገሩ ሳይመረምር የሚያስተጋባ ተቀባይ ስላለው ለምን ይጨነቃል። በዚህም የተነሳ በተስፋዬ ልብ ወለድ ኦሮሞ የሆነው በላይ ዘለቀ በኦነጋውያን ዘንድ ቅቡል ሆነ። ግጥምም ተጻፈና «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ተብሎ ተዘፈነለት። ይህ የተስፋዬ ትርክት «ምሁር ነኝ!» በሚል ልሳን ሌሎችን በድንቁርና በሚከስ አንደበት «ከኢትዮጵያ መውረድ፤ እንቦጭ፤ እንዘጭ፤ መክሸፍ ነው» በሚል ሀሳዊ ራሱ «እንቦጭ እንዘጭ» ብሎ መክሸፉንና የተስፋዬ ልሳን ደጋሚነት ባደባባይ አስመስክሯል።

በላይ ጎጃም የተወለደ ኦሮሞ ቢሆን እንኳ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ተብሎ ግጥም ይጻፋል ወይ በሚል የዘፈን ግጥም ሀያሲያንን ለመጠየቅ ሞክረን ነበር። ሁሉም የዘፈን ግጥም ሀያሲያን «ትግራይ ቢወለድም እገሌ ዐማራ ነው»፤ «ሸዋ ቢወለድም እገሌ ትግሬ ነው»፤ «ሐረር ቢወለድም እገሌ ስሜን ነው» ፤ «ናዝሬት ቢወለድም እገሌ ጋሞ ነው»፤ «ጎጃም ቢወለድም እገሌ ላስታ ነው» ወዘተ የሚል ይዘት ያለው የዘፈን ግጥም በሞያ ዘመናቸው ውስጥ እንዳላጋጠማቸው፤ ያን ዓይነት ይዘት ያለው የዘፈን ግጥም በትምህርት ቤትም እንዳልተማሩ፤ ቢጻፍም የግጥሙ ጥራት በጣም ደካማና የወረደ እንደሆነ አስረድተውናል።

ኦሮሞ የነበላይ የእድሜ አጋር የሆኑ እንደነ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ልጅ ገርቢ ቡልቶ፣ ወዘተ...ዓይነት ጀግና ኢትዮጵያውያን አርበኞችን አፍርቷል። ዘፋኙ ወይንም ግጥሙን የጻፉት የተስፋዬ ተማሪዎች «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ደካማና ሀሳብ የሌለው ዘፈን ከሚጽፉ እንደ በላይ ዘለቀ ጀግና ለሆኑት ለእውነተኛ የኦሮሞ ጀግና የኢትዮጵያ አርበኞች ለሆኑት ለነ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ለነ ኮሎኔል አብዲሣ አጋ፣ ለነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ. . . ወዘተ ትንሽ ዘፈኑን ቀየር አድርጎ ቢዘፍን፣ ዘፈኑ የእውነት ማስታወሻ ይሆን ነበር ብለውኛል።

ኦነጋውያን ዋነኞቹን እነ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎን፣ ገረሱ ዱኪን፣ አብዲሳ አጋን የመሰሉ ስመ ጥር የኦሮሞ ተወላጅ የኢትዮጵያ አርበኞች «የነፍጠኛ ተላላኪ» እና «ጎበናዎች» እያሉ እያሸማቀቁና እያዋረዱ ለምን የእነዚህ አርበኞች የዕድሜና የዘመን ወደረኛ የሆነውን ደጃዝማችን በላይ ዘለቀን ኦሮሞ አድርገው ማክበር ፈለጉ? ለነገሩ አገራችን ውስጥ ያለው የዘር ፖለቲካ ብሂል «የራስ» የሚሉትን እየጣሉና እያኮሰሱ «የሌላውን» ደግሞ ማንሳትና መንጠቅ፤ እንዲሁም ለጠብ መጋበዝ ስለሆነ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ሀሳብ የሌለውን ዘፈን መደረቱ የማይጠበቅ አይደለም።

በላይን ራሱን በአካል አግኝነተው አናግረው ታሪኩን ከሥሩ የጻፉት ደጃዝማች ከበደ ተሰማ «የታሪክ ማስታወሻ» በተሰኘው የታሪክ መጽሐፋቸው ምዕራፍ ፩፯ ገጽ ፪፻፩፫ ላይ እንደጻፉት በላይ ዘለቀ የተወለደው እዚያው ጎጃም ምድር በቢቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምጨን ከተባለው ቀበሌ ውስጥ ነው።

ይህን የሚያውቀው ሕዝብም...

እንደ ቀትር እሳት የሚፋጀው ፊቱ፣
አባ ኮስትር በላይ ለምጨን ላይ ነው ቤቱ።

ብሎለታል።

የበላይ አባትም ሙሉ ስማቸው ዘለቀ ላቀው አገኘሁ እንጂ ተስፋዬ ገብረአብ ፈልስሞ ለኦነጎች እንዳስተማረው«ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ» አይደለም።

የበላይ ዘለቀ አባት ዘለቀ ላቀው የጎጃም የለምጨንና አካባቢ ተወላጅ ናቸው። የበላይ ዘለቀ ቅድመ አያት ወይንም የዘለቀ ላቀው አያት አገኘሁ ይባላሉ። የአገኘሁ ትውልድ ቅዬ ጎጃም ውስጥ በቀድሞው አጠራር ብቸና አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ለምጨን የምትባል ወረዳ ናት። የለምጨን አዋሳኝ ወረዳዎች በረንታ፣ እነማይ፣ ሸበል፣ እናርጅ እናውጋ፣ ወዘተ ናቸው። የአገኘሁ እናትና አባት ዘመዶች የለምጨን አዋሳኝ ወረዳዎች የሆኑት የበረንታ፣ የሸበልና እነማይ ባለርስቶችና ተወላጆች ናቸው።

የበላይ ዘለቀ አያቶች ላቀው አገኘሁና እንግዳዬ ብሩ ይባላሉ። የበላይ ሴት አያት ወይዘሮ እንግዳዬ ብሩ በመንደራቸውና በቤታቸው የሚታወቁት በኃይለኛነታቸው ነበር። በብቸናዎች ዘንድ በላይ ዘለቀ የሚታወቅበት አርማው የሆነው ጀግንነቱ የተገኝው በለምጨን፣ በበረንታ፣ በእነማይ፣ በሸበል፣ በእናርጅ እናውጋና በሌሎች አካባቢዎች እየተዟዟረ ባካበተው ተሳትፎ ብቻ ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ ጉዳይ ከሴት አያቱ ከወይዘሮ እንግዳዬ ብሩ ኃይለኛነት የተወረሰ አድርገው ይቆጥሩታል። ይህን ታሪክ የሚነግሩን የበላይ ዘለቀ የቅርብ ዘመድ የሆኑት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ «ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስአበ» በሚል ባሰናዱት  የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ ስለ በላይ ዘለቀ በጻፉት ምዕራፍ ነው።      

በላይ ዘለቀን ኦሮሞ አድርገው የሚያምታቱ ግለሰቦች የኦነግ የታሪክ አዋቂውና የወያኔው ሹም  ተስፋዬ ገብረ አብ ከተናገረው ፈጠራ በስተቀር አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ የላቸውም። የበላይ አያት የለምጨኑ ላቀው አገኝሁ ከትውልድ ስፍራቸው ተነስተው በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሢሠሩና ሲኖሩ በሕግ ካገቧቸው ሚስቶችና በተለያዬ ጊዜ አብረዋቸው ከነበሩ ሴቶች ብዙ ልጆችን ወልደዋል። ይህም የሆነው እንደሚከተለው ነው።

ዳግማዊ ምኒልክ በወርኃ ጥር 1869 ዓ.ም. ደጃች ወሌ ብጡልን ለማስገበር ሠራዊታቸውንና መኳንንታቸውን ይዘው ወደ የጁና ወረይሉ ዘምተው ነበር። ደጃች ወሌም በጥር 26 ቀን 1869 ዓ.ም. ሠራዊቱንና መኳንንቱን አስከትሎ ለንጉሥ ምኒልክ ገቡ። በወርኃ የካቲት ንጉሥ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ መናገሻቸው ጉዞ ላይ ሳሉ ራስ አዳል ተሰማ በጌምድር ተሻግረው ነጋሽ ወረኛን ድል በማድረግ የስሜንን ነፍጥ ሁሉ ወሰዱት የሚል ወሬ ሰምተው ኖሮ፣ የጁና ወረይሉ የባጀውን ጦራቸውን ይዘው ደጃች ወሌን ወደ ደብረታቦር እንዲሄዱ አዝዘው፣ እሳቸው ወደ በጌምድር ተጓዙ።

ራስ አዳልም ወደ መናገሻቸው መንቆረር ተመልሰው ኖሮ፣ ምኒልክ ሠራዊታቸውን በታንኳ ዐባይን አሻግረው በደብረ መዊዕ በኩል አድርገው ወደ ራስ አዳል ከተማ ወደ መንቆረር ገሠገሡ። ንጉሡ መንቆረር ሲደርሱ ራስ አዳል በመሸሻቸው፣ ሠራዊታቸውን ይዘው በጎጃም ሲያልፉ ወታደሮቻቸው በየቦታው ለሕዝቡ ትርዒት እንዲያሳዩ በማድረግ ወደ አንኮበር ተመለሱ። የንጉሥ ምኒልክ ጦር ለጎጃም ሕዝብ ትርዒት ካሳየባቸው ቦታዎች መካከል አዴት፣ ደብረ መዊዕ፥ ደብረ ኤልያስ፣ ቀራኒዮ፣ መርጡለ ማርያም፣ ዲማና ለምጨን ይገኙበታል። አዴት ላይ የተደረገው የምኒልክ ጦር ትርዒት ተከትሎ፣ አዴት መድኃኔ ዓለሞች ካህናቱ «አርአያ ሥልጧኖ ላዕለ ምድረ ወሎ፣ ወበጌምድር ዐጼ ምኒልክ» ያሉት በሠፊው ተራብቶ የተቀሩት የጎጃም አድባራት ሁሉ በየደብራቸው ወረባቸውን እያሰናዱ ምኒልክን ለመቀበል ተዘጋጁ።

የለምጨን ካህናት «ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ አስዐሮሙ ለምድረ ጎጃም፣ ወበጌምድር ይቤ ንጉሥ ዐጼ ምኒልክ ስምዕዎኬ ለንጉሥነ ኩል ክሙ አብያተ ክርስቲያናት ዘከመ አክበሮሙ ለአድባር እንዘይብል አነ ወልደ ዳዊት» አሉ። በዚህ ለንጉሥ ምኒልክ በተደረገው አቀባበል የተደሰቱ የንጉሡ ወታደሮች ለተሰብሳቢው የአካባቢው ሕዝብ ለየት ያለ ወታደራዊ ትርዒት አደረጉ። ብዙ የለምጨን ጎልማሶችም ባዩት የንጉሥ ወታደሮች ልዩ ትርዒት በመማረካቸው የንጉሡ የዳግማዊ ምኒልክ ወታደር መሆን ተመኙ። ይህ ፍላጎት ካደረባቸው የለምጨን ጎልማሶች አንዱ ላቀው አገኝሁ ለንጉሡ የቅርብ ሰዎች ፍላጎታቸውን አሳውቀው ኖሮ፣ ተፈቅዶላቸው የንጉሥ ምኒልክን ጦር ተቀላቅለው ራስ አዳል ታየ ወደተባለበት አገው ምድር ተጓዙ።

ራስ አዳልም ከአገው ምድር በመሸሹ ዳግማዊ ምኒልክ በራስ አዳል ከተማ በመንቆረር አድርገው ጦራቸውን ይዘው ሸዋ ገቡ። የምኒልክን ጦር የተቀላቀለው ላቀው አገኘሁ ከዓመታት የማስገበር ዘመቻ በኋላ፣ ሻለቃ ተብለው የንጉሡ ቤተ መንግሥት የግቢ ዘበኛ ሆኑ። ከዚያም በሹመት የአውራጃ ገዢ ሆነው በቀድሞው ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት የኮንታ አውራጃ ገዢ፤ በቀድሞው ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የአርጆ አውራጃ ገዢ፤ በቀድሞው በጌምድር ጠቅላይ ግዛት የደብረታቦር ገዢና በቀድሞው ወሎ ጠቅላት ግዛት የጫቃታ አውራጃ ገዢ ሆነው ሠርተዋል።

ሻቃ ላቀው አገኘሁ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የአርጆ አውራጃ ገዢ በነበሩበት ጊዜ የወለጋ ተወላጅ ከሆነች ወይዘሮ ልጆችን ወልደዋል። ሻቃ ላቀው አገኘሁ ከወለጋዋ እመቤት ከወለዷቸው ልጆች መካከል ተሰማ ላቀው አንዱ ናቸው። ተሰማ ላቀው በአርበኛነቱ ዘመን ፊታውራሪ የሆኑ ሲሆኑ ዘነብ ተሰማ እና ዛሬም ድረስ በብቸና ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደር እርመድ ተሰማ የሚባሉ አዛውት አባት ናቸው። ላቀው አገኘሁ ከወለጋዋ እመቤት የተወለዷት ሌላ ልጃቸው ሴት ስትሆን ስሟ ቦጋለች ላቀው ይባላል። ቦጋለች የወለደችው ልጅ ስለሌላት ራሷን አልተካችም።

በስሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ደብረ ታቦር አውራጃ ይሠሩ በነበረበት ወቅትም፣ የባላባት ልጅ የሆነች የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪ ባለቤት የነበረችን እመቤት ጠልፈው ወደ ትውልድ ቅያቸው ጎጃም ለምጨን በመውሰድ ከዚህ ከጠለፏት ሴት ወይዘሮ የደጃዝማች አየለ ታደሰን አባት ታደሰ ላቀውንና ሶማ ሲዋጋ የወደቀውን የጀግናው ሽፈራው ገርባውን እናት አያህሉሽ ላወቀውን ወለዱ። የበላይ ዘለቀ የአክስት ልጅ ጀግናው አርበኛ ሽፈራው ገርባው በላይ ዘለቀ ከጎጃሙ አስተዳዳሪ ከራስ ኃይሉ በለው ተክለ ሃይማኖት ጋር ተጣልቶ ተከታይ አርበኞችን በመያዝ ሶማ በረሀ በወረዱበት ወቅት፣ ከመንግሥት ታጣቂዎች ውጊያ ተከፍቶ እንደ በላይና እጅጉ ዘለቀ እጅ ሳይሰጥ በጦርነት ላይ ሳለ በመሞቱ «ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው፤ ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው» የተባለለቱ ነው። ይህ ጀግና በአባቱ ከጎጃም ለምጨን ሲሆን በእናቱ ከበጌምድር ደብረ ታቦር ነው።

ወደ ቀድሞ ምድባቸው ወደ ደብረ ታቦር አውራጃ ገዢነት መመለስ የማይችሉት ላቀው አገኘሁ፤ አገልግሎታቸው ተቆጥሮላቸው በአውራጃ ገዢነት ከለምጨን ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ጫቃታ ተዛውረው በነበሩበት ጊዜ ፣ ከሕግ ባለቤታቸው ከኃይለኛዋ የጎጃም ሸበል በረንታ ተወላጅ ከወይዘሮ እንግዳዬ ብሩ የወለዱትን የመደብ ልጃቸውን ዘለቀ ላቀውን ከአካባቢው ባላባቶች ልክ ከሆነችው ከአንዷ ከጣይቱ አሰኔ ጋር ትዳር እንዲመሰርት አደረጉት። ይህ ሁሉ ታሪካዊ ክንዋኔ የተፈጸመው በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመን ነው። ላቀው አገኘሁ በጫቃታ ገዢነት ብዙም ሳይቆዩ ህመም ስላጋጠማቸው ወደ ጎጃም ለምጨን በመመለስ መሬታቸውን እያሳረሱ የአልጋ ቁራኛ ሆኑ። ልጃቸው ዘለቀ ላቀውም አባቱን ለማስታመም ወደ ለምጨን አብሮ ተመለሰ። ልጅ እያሱ አልጋወራሽ ሆኖ በእንደራሴነት ሲሾሙ ዘለቀ ላቀው ወደ አዲስ አበባ ሄዶ ለልጅ እያሱ በማደር ባሻ ዘለቀ ተብሎ እንደ አባቱ የቤተ መንግሥት ጠባቂ ሆኖ ተቀጠረ። ልጅ እያሱ ከሥልጣን ሲወርዱ ወደ አገሩ ወደ ለምጨን ተመለሰ።

ጎጃም እንደተመለሰም ከልጅ እያሱ ከሥልጣን መውረድ ጋር ተያይዞ ፣ በለምጨን፣ በበረንታ፣ በእነማይ፣ በሸበል ፣ በእናርጅ እናውጋ የሕዝብ አመጽ በመነሳቱ ከሥራው የተባረረው ዘለቀ ላቀውም አመጸኛ ሆኖ ጫካ ገባ። በዚህ ጊዜ በቢቸና የራስ ኃይሉ ተክለ ኃይማኖት ሌባ አዳኝ በነበሩት ፊታውራሪ እምቢያለ ውዱ ተከበበ። ዘለቀ ላቀውም «እጄን አልሰጥም!» በማለቱ ተኩስ ተከፈተ። ዘለቀ ላቀውና አብረዋቸው የነበሩ ወንድማቸው ከአስር ሰው በላይ ገድለው ብዙ ሰው አቆሰሉ።

በመጨረሻ ከፊታውራሪ እምቢያለ የተተኮሰች አንድ ጥይት ዘለቀ ላቀው ላይ አረፈችና ሕይወቱ አለፈች። አብረውት ሲዋጉ የነበሩ ወንድሞቹ እነ ታደሰ ላቀው፣ አበጀ ላቀውና ዓለሙ ላቀው ግን በተኩስ ልውውጥ ተመትቶ የሞተውን የወንድማቸውን ናስማስር ይዘው አመለጡ። ዘለቀ ላቀው ሲሞት ባለቤቱ ጣይቱ አሰኔ ልጆቻቸውን በላይና ታናሹን እጅጉ ዘለቀን ይዛ ወደ ወላጆቿ ቅዬ ወደ ጫቀታ ተመለች። ይሄ የሆነው ታህሳስ 1916 ዓ.ም. ነበር። በላይ በዚህ ጊዜ የ14 ዓመት ልጅ ነበር። በመጨረሻም በላይ ዘለቀ ያባቱን ደም ለመመለስ አጎቶቹ ይዘውት የሸሹትን የአባቱን ናስማስር ውዥግራ ጠመንጃ ይዞ ቢቸና ሸፈተ። ቢቸና በሽፍትነት ሳሉ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ወረረች። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ለሽፍታ ሁሉ ምሕረት አድርገው ጥሊያንን እንዲዋጋ ባስነገሩት አዋጅ መሠረት እነ በላይ የፀረ ፋሽስት አርበኝነት ትግሉን ተያያዙት።

ከፍ ብሎ የቀረበው ታሪክ ምንጮች አንደኛ፡ በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴየተጻፈውና በ1959 ዓ.ም. የታተመው «ታሪከ ነገሥት ዘዳግማዊ ምኒልክ» የሚለው የዳግማዊ ምኒልክ ዜና መዋዕል፤ ሁለተኛ በደጃዝማች ከበደ ተሰማ ተጽፎ በ1963 ዓ.ም. የታተመው «የታሪክ ማስታወሻ» ሁለተኛ እትም መጽሐፍ ገጽ ፪፻፩፫፤ በዶ/ር ለይኩን ብርሃኑ የተጻፈ [ያልታተመ] «ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ» ድርሳን ከገጽ 25-43 እና ሶስተኛ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በ2008 ዓ.ም. ያሳተሙት «ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስአበባ» መጽሐፍ ከገጽ 77-85 ናቸው።

እንግዲህ! የበላይ የዘር ሐረግ ከፍ ብሎ የቀረበውን ይመስላል። የበላይ አባት ዘለቀ ላቀው አገኘሁ የጎጃሙ ተወላጅ የለምጨኑ የላቀው አገኘሁና የጎጃሟ ተወላጅ የሸበል በረንታዋ የወይዘሮ እንግዳዬ ብሩ ልጅ ናቸው። እርግጥ ነው፤ ላቀው አገኘሁ ወለጋም፣ በጌምድርም፣ ወሎም፣ ሲዳሞም በሥራ በሄዱበት ሁሉ ልጆችን ወልደዋል። የበላይ አባት ዘለቀ ላቀውን ግን የወለዱት ከጎጃም ተወሏጇ ከሸበል በረንታዋ ከእንግዳዬ ብሩ ነው። ስለዚህ የበላይ አባት ዘለቀ ላቀው በእናቱም አባቱም የዚያው የጎጃም የለምጨንና የሸበል በረንታ ተወላጅ እንጂ እነ ተስፋዬ ገብረአብ ፈጥረው እንደሚያወሩት «ቂልጡ አያኖ ገልገሊ» የሚባል ኦሮሞ አይደለም።

ኦሮሞነቴን «በሕግ አስከብሬያለሁ» የሚለው ተስፋዬ ገብረ አብ የበላይን አስከሬን ኦሮሞ ከባንቱ በወረሰው በሞገሳ ባህል መሠረት ኦሮሞ አድርጎት ካልሆነ በስተቀር በሕይዎት የነበረው በላይ ዘለቀ እውነተኛ ታሪክ ይህ ከላይ የቀረበው ነው።

እንኳን የበላይ ዘለቀ ማንነት ከላይ በቀረበው መልኩ ጥርት ብሎ ተመዝግቦና ታሪኩ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሆኖ ሳለ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ እንኳ ማንነት ዋናው ባለቤቱ የሚወስነው መለያ እንጂ፣ አንድ ሰው ከሞተ ከሰባ አንድ ዓመት በኋላ ማንም የተስፋዬ ተማሪ እየተነሳ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» በማለት የሚደርተው ጨርቅ አይደለም። ያገራችን ዘረኞች ግን የራስ አገር የመፍጠር ትግሉ አልሳካ ሲላቸው፣ የታሪክና የማንነት ሽሚያ ላይ ተሰማርተው ዘፈኑን፣ ታሪኩንና ግጥሙን ሁሉ በብሽሽቅ አጨማልቀውት ፌስቡክ ላይ ታሪክ ለሚማረው የዘመኑ ትውልድ የታሪክን እውነትና ውሸት መለየት እንዳይችል አድርገው አወሳስበውበታል። የሆነው ሆኖ በላይ ዘለቀ የጎጃም ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ጀግና አርበኛ ነው። በአርበኝነት ዘመኑ ድንቅ ሀሳብ የሰፈረበት ማህተም ነበረው። ከታች የታተመው የበላይ ክብ ማህተም...

«በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያ ደም መላሽ» ይላል።

እሱም ሲፈርም «በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያ ደም መላሽ፤ እንባዋን አባሽ፤ ጣሊያንን ደምሳሽ» ብሎ ነበር። የበላይ ማንነት ይህ ነው። ከዚህ የተለየ ማንነት የለውም። በላይ በዚህ መልክ ራሱን ስለገለጸ ዛሬ ሺህ ተስፋዬ የፈለገውን ቢደርትና አገር ለማዳን ተሰበሰብን እያሉ አገራችንና የሞቱላትን ባለታሪኮች ለምንደኛ በአግቦ የሚያቀርቡ ምሑር ነን ባይ ሁሉ ቢራኮት በላይን ሌላ ሊያደርገው አይችልም።

ከበላይ ጋር በጀግንነት አብሮ የተዋደቀው የጎጃም ሰው ለበላይ ከገጠመለት አያሌ ሙገሳዎች ከፊሎቹ የሚከተሉት ናቸው...

ጎጃም ባርበኝነት እንደምን ታወቀ፣
ያ በታች ዝቅ ሲል ያ በላይ ዘለቀ፤
***

ያ በላይ ዘለቀ የለምጨን በርበሬ፣
ጠላት ተሸበረ እየሰማ ወሬ፤

***
ጎጃም ዓይኑን ታሞ ሲደነባበር፣
የለምጨኑ አንበሳ ይመራው ጀመር፤

*** 
የለምጨኑ አንበሳ፣ 
መጣሉ እያገሳ፤
የሸበል ንጉሥ፣
ገባሉ ማርቆስ።

***
አባ ኮስትር በላይ የለምጨኑ አንበሳ እባክህ ተቆጣ፣
አንተም ራስ ተባል እኛም ጎጆ እንውጣ፤

***
ፈረንጅ ምድር ለቆ ቢሄድ በሰማይ፣
የጎጃሙ አንበሳ ዳመናውን አልፎ ዘለቀ በላይ።

*** 
ጣሊያን ፍየል ሆኖ ቅጠል ቅጠል ሲያይ፣
የለምጨኑ አንበሳ ነብር ተመስሎ አረደው በላይ።

*** 
የጎጃሙ ነብር የለምጨኑ አንበሳ፣ 
አባ ኮስትር በሌ እንደምን ይረሳ።

*** 
ሰላሳ ደጃዝማች አምሳ ፊታውራሪ ያስቀመጠውን፥ 
ጭልጥ አርጎ ጠጣው በላይ ብቻውን። 
*** 
ያ በላይ ዘለቀ የጦር አጋሠሥ፣ 
ባንድ ቀን ያስገባል መቶ መትረየስ። 
***

በኋላ ከአዲስ አበባ ከእስር አምልጦ ወደ ጎጃም ሲሄድ ሱሉሉታ ላይ መያዙን የሰማው የጎጃም ሰው ያ ጥይትና ጦር በያይነት የነበረው አርበኛው ጥይትና ሽመል አጥቶ ሳይዋጋ ለሚያሳድዱት እጁን መስጠቱን በተረዳ ጊዜ ...

ጥይት አልቆብህ፣ ድንጋይ ተቸግረህ፣ ሽመል ተቸግረህ፣
አወይ ወንድም ወንድም አወይ አገር አገር አላለም ወይ ልብህ፤

በማለት በላይ ተዋግቶ እንዲያመልጥ በቦታው ተገኝቶ ጥይትና ሽመል ለጀግናው ባለማቅረቡ የተሰማውን ቁጭት ገልጿል።

በመጨረሻም የበላይ መሰቀል በጎጃም ሲሰማ...

የአባ ጠቅል ሀሳብ ማሰልጠን ነበረ፣ 
ሌት ተቀን ሳያርፉ ማስተማር ነበረ፣ 
ምኑን ሠለጠንነው ጀግናው ካልተማረ።

*** 
ያ በላይ ዘለቀ ታላቁ ዝሆን፣
ጦር መጣልህ በሉት፣ ይነሳ እንደሆን፤

***
የሺፈራው እናት አይዞሽ አታልቅሺ፣
የልቡን ሠርቶ ነው የሞተው ልጅሺ፤

***
ተንግዲህ ወንድ አለ ብየም አላወራ፣
ጀግንነቱ አለቀ ካባኮስትር ጋራ። ብሎ ነበር!

በርግጥ በላይ ዘለቀ ጀግና ነበር። በርግጥም «የኢትዮጵያ ደም መላሽ፤ እምባዋን አባሽ፤ ጣሊያንን ደምሳሽ» ነበር። የበላይ እውነት ይሄ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ እውነታ የለውም!

ከታች የታተሙት ታሪካዊ ምስሎች የበላይ ዘለቀን ትክክለኛ ገጽታ የሚያሳይ ፎቶና በላይ  ይጠቀምበት የነበረው ማኅተም ነው።